ቀጥታ፡

የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ ቴክኖሎጂ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነታቸውን የበለጠ እንዲወጡ ያግዛል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና የአስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሥራቸውን በኃላፊነት ስሜት የበለጠ እንዲያከናውኑ እንደሚያስችል የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያለማውን የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ በይፋ ሥራ አስጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በርካታ ተቋማትን እየደገፈ ይገኛል።

ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዛሬው ዕለት ወደ ሥራ የገባው የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ ለሚዲያው ዘርፍ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በተለይ ግልጽነትና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነትን በተላበሰ መንገድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።


 

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው፤ የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓቱ የማኑዋል አሠራርን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንዲሁም ለሚዲያዎች ራሱ እንደ ግብረ መልስ ያገለግላል ብለዋል።


 

የኤን.ቢ.ሲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂው የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያረጋግጥና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በመገናኛ ብዙኃን መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዲ፤ ቴክኖሎጂው ተጠያቂነት ያለው አሠራርን የሚያረጋግጥ፣ ሥራን የሚያቃል፣ ግልጽነትን የሚፈጥርና የተቋሙን ውጤታማነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በመርሐ ግብሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፣ የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም