የክልሉን ከተሞች ከተፈጥሮ ፀጋዎቻቸው የሚያሰናስል የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ከተሞች ከተፈጥሮ ፀጋዎቻቸው የሚያሰናስል የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተሞችን ከተፈጥሮ ፀጋዎቻቸው የሚያሰናስል አስደናቂ የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎችና ኢንቨስትመንት ምቹ ምኅዳር በመፍጠረ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም አሶሳ ከተማን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችን በኮሪደር ልማት በማስዋብ ለነዋሪዎችና ኢንቨስትመንት ምቹ ምኅዳር የመፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን የመሰረተ ልማት ፍላጎትን በማሟላት ውብ ገፅታ እያላበሳት መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት የለውጡ መንግስት የከተሞችን ዳግም ውልደት ያበሰረበት ወሳኝ የልማት መርሃ ግብር መሆኑን አንስተዋል።
ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የክልሉን ከተሞች መሰረተ ልማት በማሳለጥ ውብ ገፅታ እያላበሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የኮሪደር ልማት ስኬቶችን የበለጠ በማስፋት ከተሞችን ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በክልሉ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎችም የክልሉን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፀጋ በመጠቀም በተለያዩ መስኮች በስፋት እየተሰማሩ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራት ለሚሹ አልሚዎች ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ በቁርጠኝነት እደሚሰራ አረጋግጠዋል።