በክልሉ ለኩታ ገጠም እርሻ በተሰጠ ትኩረት በምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለኩታ ገጠም እርሻ በተሰጠ ትኩረት በምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) ተናገሩ።
ክልላዊ የበልግ አዝመራ የመስክ ምልከታ መርሃ ግብር በወላይታ ዞን ዳሞት ፑላሳ ወረዳ ተካሂዷል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ በበልግ አዝመራ 987 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር በመሸፈን ከ97 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በበልግ ወቅት እየለማ ካለው መሬት 354 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም እርሻ እየለማ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ አርሶ አደሩን በዘመናዊ እርሻ በማሳተፍ ወደ ሜካናይዜሽን እርሻ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።
በተለይ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የኩታ ገጠም እርሻ ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በርካቶችን ውጤታማ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በበልግ አዝመራ በማህበር ተደራጅተው በኩታ ገጠም እርሻ ያለሙትን በቆሎ እየተንከባከቡ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደር ኤርጋና ኤርሳዶ ናቸው።
ወረዳው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ግብአቶችን ቀድሞ ማድረሱ ሥራቸውን ውጤታማ እንዳደረገው ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር በዘነ ሀርኪሶ ምርጥ ዘር፣ ዩሪያ እንዲሁም ዳፕ ማደበሪያዎችን ቀድመው በማግኘታቸው የበልግ ወቅት የሰብል ልማት ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህም ያለሙት በቆሎ ቡቃያ በጥሩ ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው የግብርና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለው ድጋፍና ክትትል ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።