ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶች ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ግብዓት እንሆዲኑ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶች ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ግብዓት እንሆዲኑ እየሰራ ነው
አምቦ፤ ሚያዝያ 23/ 2018 (ኢዜአ)፦ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንስ ጋር በማቀናጀት ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ግብዓት እንዲሆኑ በጥናት እያገዘ መሆኑን አስታወቀ ።
አምቦ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶች ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ቃል 11ኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ እይካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንገለጹት ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ነው።
በተለይም በምርምር ስራዎቹ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ተጨባጭ ችግሮች እንዲፈቱ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጤና፣ በግብርና፣ በባህልና በአስተዳደር ዘርፎች ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ግብዓት እንዲሆኑ የጥናት ውጤቶችን እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የዛሬው የምርምር ከንፍረንስም የማህበረሰቡን ሀገር በቀል እውቀትን በማጥናት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማስተሳሰር ችግር ፈቺ የሚሆንበትን አቅም ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ማሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዘንድሮው ኮንፈረንስ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት የተውጣጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች ያጠኗቸው በርካታ የጥናት ፅሁፎች ለውይይት እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።
የቀረቡት ጥናቶች በዋናነት ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ትኩረት ያደረጉና በተግባር ሲተረጎሙም የህብረተሰቡን የእለት ተእለት ችግር የመፍታት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮንፈረንሱም እውቀቶቹ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ተቀናጅተው ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሂደት ለማቀላጠፍና በተመራማሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የታደሙ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ በተመረጡ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።