ቀጥታ፡

በዞኑ የተከናወኑ የልማትና የህግ ማስከበር ስራዎች የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ናቸው

ደብረብርሃን፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የልማትና የህገ ማስከበር ስራዎች የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ገለጹ።

የሰሜን ሸዋ ዞንና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የዘጠኝ ወር የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻፀማቸው ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዞኑን ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የተሳካ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል።


 

በተለያዩ መድረኮች ማሕበረሰቡን በማወየየትም የመንግስትን የሰላምና የልማት ተግባራት እንዲገነዘብ በመደረጉ በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፉን መስጠቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም በርካታ የታጠቁ ሀይሎች አመራሮችና አባላት የሰላም አማራጭን በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በአካባቢው የተገኘው ሰላም የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የልማት ስራዎችን በማከናወን የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን 19 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ለ54 የኢንቨስትመንት ፕሮጀከቶች ለግንባታ የሚውል መሬት መስጠት መቻሉን ጠቁመው በዚህም ለ13 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

መሰብ የአንድ ማዕከል ህንጻ ግንባታን በማፋጠን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚሁ ወቅት በማህበር ተደራጅተው የቆጠቡና ሌሎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ላሟሉ ከአምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም