ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አስደናቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው - አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አስደናቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በአረንጓዴ አሻራ፣ የውሃ፣ የንፋስና የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ምንጮችን በማስፋፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያስገኘ ዕድገት እያመጣ ይገኛል።

የበካይ ጋዝ ልቀትን የሚቀንሱ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የትራንስፖርት አማራጮችን ማበረታታትና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዘላቂ ግብርናን የሚያሳልጡ ስትራቴጂክ የልማት አቅጣጫዎች ናቸው።

ይህ የተቀናጀ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅና ዕድገትን በማፋጠን ለቀጣዩ ትውልድ አስተማማኝ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የአየርለንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተለያዩ የትብብር መስኮችን በማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ተምሳሌትና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ስኬቶችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በተለይም በታዳሽ ኃይልና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተመዘገቡ ውጤቶች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ መሠረቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም አየርላንድ የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮ-አየርላንድን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው የልማት መስኮች በአጋርነት እየተሰራ አንደሚገኝም አምባሳደሯ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና አየርላንድ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የበለጠ በማጠናከር በተለያዩ የልማት መስኮች የሚደረጉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር እንደምታጠናክርም አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም