ቀጥታ፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል

አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ በአርባ ምንጭ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ለመያዝ የተወጡትን ሃላፊነት በምርጫው ቀንም ድምጻቸውን በመስጠት ለመድገም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ያላቸውን የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለይተው ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።  
 

አስተያታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አለማየሁ በቀለ እንዳሉት በጠቅላላው ምርጫ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ለመምረጥ የፓርቲዎችን ክርክርና የፖሊሲ አማራጮች ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ይህም ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ መጎልበትና ለህዝብ የልማት ተጠቃሚነት በተሻለ ይሰራል ብለው ያሰቡትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመለየት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የምርጫው ስኬታማነት በዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚወሰን በመሆኑ የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በምርጫው ቀን ድምጻቸውን ይበጀኛል ላሉት ፓርቲ በመስጠት ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

"ለመምረጥ የሚያስችለኝን ካርድ ወስጄ የድምፅ መስጫ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው" ያለችው ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወጣት ሀና ሸዋ ናት።

የምመርጠውን ፓርቲ በስሜት ሳይሆን በጥንቃቄ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያለችው ወጣቷ፣ በተለይ በቀጣይ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማት በማፋጠን ህዝብን ተጠቃሚ ለሚያደርግ ፓርቲ ድምጿን ለመሰጠት መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ይበጃል፤ ሀገርንም ያሻግራል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ኦሳ ፋንታ ናቸው።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እንዲያስተዋውቁ መመቻቸቱ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት የእኔ አንድ ድምጽ ዋጋ አለው ያሉት ነዋሪው፣ በምርጫው ቀን ካርዳቸውን በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ከመጠቀም ባለፈ ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።  

ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም