በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪው ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለምጣኔ ሃብት እድገት ጠንካራ መሰረት እያኖረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪው ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለምጣኔ ሃብት እድገት ጠንካራ መሰረት እያኖረ ነው
ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪው ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለምጣኔ ሃብት እድገት ጠንካራ መሰረት እያኖረ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
"ኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ በደብረ ብርሃን ከተማ የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት አቅማቸውን የማሳደግና በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባት የቻሉበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩ ተነስቷል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪው ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለምጣኔ ሃብት እድገት ጠንካራ መሰረት እያኖረ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ከአርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ፣ የግብአት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታትና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለዘርፉ እድገትና ማንሰራራት በትጋት መሰራቱን አንስተዋል።
በተለይም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ የቢራ ገብስ፣ ጥጥና ሌሎች ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ግብአት እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ዘርፉ ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለምጣኔ ሃብት እድገት ጠንካራ መሰረት እያኖረ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችም ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
መሰል መድረኮች የዘርፉን ልማት ለማሳለጥና የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት ወሳኝ መሆናቸውን የገለጹት በማምረት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ አብርሃም እና ወይዘሮ ትንሳኤ ፍቃደ ናቸው።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት የመንግስት ጥረት፣ ድጋፍና ክትትል የሚደነቅ መሆኑን አንስተው በዚህም ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ማንሰራራት ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።