የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ለ4ኛ ጊዜ የሚካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ዓለምአቀፍ ኤክስፖን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎች መፍትሔ በመስጠት የምርታማነት አቅምን እያጎለበተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖም "ኢትዮጵያ ታምርት፤ ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 25 እስከ 30/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የኤክስፖ ዋና ዓላማም የኢትዮጵያን ምርቶች በማስተዋወቅ፣ ፈጠራን ማበረታታት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥን በመፍጠር ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም ለዓለም በማስተዋወቅ የምርት ጥራትና ብዛትን የሚያሻሽል ልምድና ተሞክሮ የሚቀመርበት መሆኑንም አንስተዋል።
በኤክስፖው 850 የንግድ ስምምነቶችን በማድረግ ከአምስት ቢሊየን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ አዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚቆየውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ150 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎች እንደሚጎበኙት አስታውቀዋል።
ስታርታፖችም በኤክስፖው የሚሳተፉበትን ዕድል በማመቻቸት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ከትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲያስተሳስሩ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኤክሰፖው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የፓናል ውይይቶች፣ የምርት ልማት ውድድሮች፣ የዕውቅና እና ሌሎች መርሃ-ግብሮች እንደሚከናወኑ በመግለጫው ተመላክቷል።