ቀጥታ፡

ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት በጥራት ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የተጀመረው የገበያ ትስስር ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚተዳደረው የላሜ ዴይሪ ያስገነባውን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤ ፋብሪካው የግሉ ዘርፍ በአግሮ-ኢንዱስትሪው ያለውን ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥራቱን የጠበቀ የወተት ምርትን በዓይነትና በብዛት ለከተማዋና ለሀገሪቱ ተጠቃሚዎች በስፋት በማቅረብ፣ የነባሩን የላሜ ዴይሪ ተደራሽነት እንደሚያሰፋም አመልክተዋል።

በርካታ የቀንድ ከብት ቢኖርም በእሴት ሰንሰለት እና በምርታማነት ውስንነት ምክንያት የወተት አቅርቦቱ ላይ አሁንም እጥረት እንዳለ ተናግረዋል።

ዛሬ በላሜ ዴይሪ የታየው ዘመናዊ በሆነ ሂደት የወተት ምርትን በብዛትና በጥራት እንዲሁም ጤናማና ያለ ማቀዝቀዣ ከ6 ወራት በላይ ሊቆይ በሚችል መልኩ ለገበያ የሚያቀርብ በመሆኑ በዘርፉ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር በእጅጉ ያቃልላል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት በጥራት ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የተጀመረው የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ከንቲባዋ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም