የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን በማሳካት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚተዳደረው የላሜ ዴይሪ ያስገነባውን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ በሀገራችን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም፥ በወተት ምርትና ምርታማነት እንዲሁም አቅርቦት ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ደግሞ ዜጎች በቂ የወተት ምርት እንዳያገኙ በማድረግ በስርዓተ ምግብ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው በመገንዘብ መንግሥት ለዘላቂ መፍትሔ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትውልዱ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝና ጤናማና አምራች እንዲሆን የወተት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ላሜ ዴይሪ ባለፉት ጊዜያት በወተትና በወተት ተዋጽኦ አቅርቦት ላይ የራሱን አወንታዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱንም ጠቁመዋል።
በዛሬው እለት የተመረቀው ፋብሪካ የድርጅቱን የወተት ማምረት አቅም በተደራሽነትና በጥራት እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በቀጣይም መሰል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ከተማ አስተዳደሩ ዘርፉን ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተሟላለት ይህ ፋብሪካ የድርጅቱን የአገልግሎት ጥራት እንደሚያሳድግ ጠቅሰዋል።
ፋብሪካው የወተት ተዋጽኦን ያለምንም ማቀዝቀዣ ለስድስት ወራት ማቆየት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በምረቃ መርኃ-ግብሩ ለወተት አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ሌሎች በዘርፉ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተበርክቷል፡፡