በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እያደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እያደገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ከፍትኛ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍጹም ከተማ ገለጹ።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የጵንኤል ኢንዱስትሪ ቆርኪ ፋብሪካ ማስፋፊያ ተመርቆ ሥራ በጀመረበት መርኃ ግብር ላይ ነው።
ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት ለውጭ ኢንቨስተሮችና ለውጭ ገበያ ብቻ ታስበው የተገነቡ ቢሆንም አሁን ግን የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ የኢንዱስትሪው መሠረት እንዲሆን አዲስ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።
በተደረገው የፖሊሲ ለውጥና ማበረታቻ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በፓርኮች ውሰጥ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጵንኤል ኢንዱስትሪ በቆርኪ ምርትና በብረታብረት የጀመረው የማስፋፊያ ሥራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ጵንኤል ኢንዱስትሪ ላሳየው ውጤት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ሌሎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መንግሥት አስፈላጊውን መሠረተ ልማትና ድጋፍ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጵንኤል ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ ብርቱካን አበበ በበኩላቸው፥ ኢንዱስትሪው ባከናወናቸው ተከታታይ የማስፋፊያ ሥራዎች የቆርኪ ማምረት አቅሙን ወደ 4 ቢሊየን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ቀጣይ የሀገር ውስጥ የቆርኪ ፍላጎትን መቶ በመቶ ለማሟላት እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት በትጋት እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተመረቀው ማስፋፊያ ዘመናዊ የብረታብረት ህትመት (Metal Package Printing) ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል ታትመው ከውጭ ይገቡ የነበሩ (Metal Sheets) በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ያስችላል ብለዋል።
መንግስት ለፋብሪካው የተለያዩ ማበረታቻዎችን ሲያደርግ እንደነበር አንስተው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።