በክልሉ በዘጠኝ ወራት ከ57 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዘጠኝ ወራት ከ57 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ57 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዐቢይ አንደሞ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት የአካባቢውን ጸጋዎች በመጠቀም ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 52ሺህ ሥራ አጥ ዜጎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ57 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከዕቅድ በላይ ለማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
በሥራ አጥ ልየታና በስምሪት ሥራ ላይ ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሳቸው በአፈጻጸሙ ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉንም ተናግረዋል።
እንደ ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጻ ለተደራጁ ወጣቶች ከ658 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ብድር የማሰራጨት፣ የመሥሪያና መሸጫ ቦታ የማመቻቸት እንዲሁም የእርሻ ማሳ የማስተላለፍ ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ ተከናውኗል።
ከዚህ ባሻገር 15 የእርሻ ትራክተሮች እና 12 የጡብ ማምረቻ ማሽኖች በክልሉ መንግሥት ተገዝተው ለወጣቶች መቅረባቸውን አክለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራው ክህሎት መር እንዲሆን ሥልጠና በማዘጋጀት የወጣቶችን አቅም የማሳደግ ሥራ በቢሮው በኩል መከናወኑንም ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በግብርናና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ያለውን ሰፊ አቅም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ነው።
በክልሉ ሚዛን አማን ከተማ ተደራጅተው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል የ"ይቻላል የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ማኅበር" ሰብሳቢ ዳንኤል ገዛኸኝ ከኮሌጅ ተመርቆ እንደ ወጣ በማህበር ተደራጅቶ ሥራ መጀመሩን ተናግሯል።
መንግስት የመሥሪያ ቦታ በመስጠትና የገንዘብ ብድር በማመቻቸት ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጾ፣ በማኅበሩ ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ተናግሯል።
የማህበሩ አባላት በዚህ ሥራ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ በቀጣይ ሥራውን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የማሳደግ ራዕይ መሰነቃቸውንም አመልክቷል።
በዶሮ ጫጩት እርባታ ሥራ የተሰማሩት ወጣት ቅድስት መኳንንት እና አቤነዘር ዳዊት ከመንግሥት የ250 ሺህ ብር የሥራ ማስጀመሪያ ብድር ወስደው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ በላይ የዶሮ ጫጩቶችን በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ሥራችውን ለማስፋፋት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።