ቀጥታ፡

ሀገራዊ የሪፎርም ተግባራት ለሠራተኞች ምቹ ምህዳርን በመፍጠር የኢንዱስትሪ ምርታማነትን እያጎለበቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ  የሪፎርም ተግባራት ለሠራተኞች ምቹ ምህዳርን በመፍጠር የኢንዱስትሪ ምርታማነትን እያጎለበቱ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሠራተኞችና አሠሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን "የሠራተኛው መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሠላም እና ለምርታማነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ እያከበረ ይገኛል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ የሀገርን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሥራና ክህሎት ዘርፍ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክህሎት ማሳደጊያና ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢ መፍጠር የሪፎርሙ ቀዳሚ ትኩረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ከአሠሪና ሠራተኛ ምህዳር ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሠራተኛውን የሥራ ሁኔታ ከማሻሻል ባለፈ፣ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ጥበቃ መስፈርቶችን በማዘመን ረገድ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም እንዲሁ።

የሥራ ገበያ ተቋማትን ይበልጥ ውጤታማና ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመረው ጥረትም ውጤታማ ነው ብለዋል።

እነዚህን እቅዶች በስኬት ለማጠናቀቅና የምርታማነት ግብን ለመምታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍና የጋራ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን አቶ ዳንኤል ተሬሳ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፤ የሠራተኞች መብት መከበር ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላምና ለምርታማነት ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ኮንፌዴሬሽንኑ ሠራተኞች ተደራጅተው መብትና ጥቅማጥቅሞቻቸው ተጠብቀው ለዘላቂ ሀገራዊ ዕድገት ሚናቸውን እንዲወጡ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፥ መምህራን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የጎለበቱ ዜጎችን በማፍራት የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

የመምህራን መብትና ጥቅሞች እንዲከበሩና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ምቹ የሥራ ከባቢ እንዲፈጠርላቸዉ ማህበሩ በስፋት እየሠራ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።

ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት ማህበሩ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም