ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት ተሰጥቷል

ነቀምቴ፣ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ) በምስራቅ ወለጋ ዞን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደረጄ ነጋሳ እንደገለጹት፣ በዞኑ የግብርናውን  ስራ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዞኑ በተለይም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል ።

ከዚሁ ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ የግብአት አጠቃቀም ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው በአጠቃላይ በትራክተር አቅርቦት፣ በምርጥ ዘር፣ በማዳበሪያ እንዲሁም በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግብርና  ቴክኖሎጂ አቅርቦቱ  የአርሶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ  ጊዜን፣ ጉልበቱና ገንዘቡን መቆጠብ እንዳስቻለም አክለዋል። 

ተግባሩን በማስቀጠል  በ2018/19 ምርት ዘመን መኽር ወቅት  801 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ያነሱት ሀላፊው በእስካሁኑም  333 ሺህ ሄክታር መሬት  መታረሱን አንስተዋል።

በምርት ዘመኑ  ከሚለማው መሬትም  225 ሺህ ሄክታሩ በሜካናይዜሽን እንደሚለማ ጠቁመው ለዚህም  ቀድሞ ስራ ላይ ካሉት በተጨማሪ 55 ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

በምርት ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት 24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የግብርና ሜካናይዜሽንን በመጠቀምና ኩታ ገጠም አስተራረስን በመተግበር ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ አርሶ አደሮች መካከል ማቴዎስ አረጋና  አያና ጎበና  እንዳሉት፤ ባለፉት አመታት የግብርና ስራቸውን ለማሳካት በኩታ ገጠም መሬታቸውን አልምተዋል።

ይህም በባህላዊ መንገድ ከሚያገኙት ምርት በእጥፍ የጨመረ በመሆኑ  በዘንድሮው አመትም በጋራ መሬታቸውን በትራክተር እያረሱ መሆኑን ተናግረዋል። 

ስራውን ይበልጥ ለማሳደግም ተደራጅተው  መንግስት ባመቻቸላቸው ብድር ትራክተር  መግዛታቸውን  ጠቁመዋል።

ዘመናዊ እርሻው የምርት ብክነትን ለመቀነስና በሰው ጉልበት በመስራት የሚባክን ጊዜን ለመቀነስ እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ተስፋ ስንሻው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር  በመደራጀት በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት ትራክተር  በመግዛት መሬታቸውን እያረሱ  መሆናቸውን  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም