ቀጥታ፡

በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ጊዜና ጉልበትን ቆጥቧል        

ወልቂጤ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብር አሰባሰብ ሥርአት ጊዜና ጉልበታቸውን እንደቆጠበላቸው ግብር ከፋዮች ገለጹ።   

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የዘረጋው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብር ክፍያ ሥርአት ግልጸኝነትና ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ጊዜና ገንዘባቸውን መቆጠብ እንዳስቻላቸው በክልሉ የሚገኙ ነጋዴዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል በወልቂጤ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ባይከዳኝ ገብሩ እና አቶ አብድልሃሚድ አብድልካፍ እንዳሉት ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

ቢሮው የዘረጋው በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሥርአት ነጋዴው ግብሩን በፍትሃዊነት፣ በግልጽነትና ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ መክፈል እንዲችል ዕድል መስጠቱንም ጠቁመዋል።

ዘመናዊ አሰራሩ ግብራቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ መክፈል እንዳስቻላቸው ገልጸው፣ ይህም ጊዜና ጉልበታቸውን ለመቆጠብ እንዳገዛቸው አመልክተዋል። 

ግብር መክፈል ለሁለንተናዊ ልማትና እድገት ወሳኝ በመሆኑ በየዓመቱ የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት መክፈላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በተሰማሩበት የሆቴል ሥራ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ለሀገር ልማት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ የቡታጀራ ከተማ ነዋሪው አቶ ኑሩ ደድገባ ናቸው።

የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ በቴሌ ብርና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች መደገፉ እንግልትን በማስቀረት ጊዜያቸውን ለመቆጠብ እንዳስቻላቸው አክለዋል፡፡

የሚሰበሰበው ገቢ በከተማዋ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን በተጨባጭ በማየታቸው ግብራቸውን በታማኝነት ለመክፈል እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል። 

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይድረሱ ተስፋዬ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ መታገዙ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት አግዟል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆኑና ከሌሎች የገቢ አርዕስቶች ከ810 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ299 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም አመልክተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቀመሪያ ረሻድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የገቢ አሰባሰቡን በማዘመንና የገቢ አማራጮችን በማስፋት ልማትን ለማፋጠን እየተሰራ ነው።

የገቢ አሰባሰቡ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መደረጉ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፣ የገቢ ሕጉን ባላከበሩ አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የስነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 72 ባለሙያዎች እና የገቢ ሕጉን ባላከበሩ ከ700 በላይ ግብር ከፋዮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡  

የገቢ አሰባሰቡን በማዘመን በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 27 ቢሊዮን ብር ገቢ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም