ቀጥታ፡

በክልሉ የቡና ልማትን በማጠናከር የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ሀላባ ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ልማትን በማጠናከር የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ፡፡

ክልላዊ የበልግ ወቅት የቡና ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀላባ ዞን ዌራ ወረዳ አለምጤና ቀበሌ ተካሂዷል፡፡


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር እንዳሉት በክልሉ የቡና ሽፋንን ለማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ ሊተገበር የሚችል ኢንሼቲቭ ተቀርፆ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

በዚህም ጥራት ያለውና ምርታማ የቡና ችግኞችን በማልማት የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ለተግባራዊነቱም 44 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ሃላፊው፣ ይህም  የክልሉን የቡና ሽፋን ወደ 180 ሺህ ሄክታር ያሳድገዋል ብለዋል።

የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶፊቅ ጁሃር በበኩላቸው፣ በክልሉ ኩታ ገጠም የቡና ልማት ሥራ በማከናወን በልማቱ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በክልሉ 169 ሺህ ሄክታር ማሳ ቡና በማልማት ምርቱ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ያሉት ደግሞ የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን ናቸው። 

ቀደም ሲል የዞኑ የቡና ሽፋን ዝቅተኛ እንደነበር አንስተው ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት 298 ሄክታር ማሳ በቡና ማልማት ተችሏል ብለዋል።


 

ቡናን ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ስለመምጣቱ የተናገሩት ደግሞ በተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት በሃላባ ዞን ዌራ ወረዳ ዓለም ጤና ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ኢመም ሰልማን ሰላቶ ናቸው፡፡

የቡና ልማቱን ከሌላ የግብርና ሥራቸው ጋር አጣምረው በማከናወን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም