በዞኑ የእንሰት ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የእንሰት ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው
ዲላ ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በጌዴኦ ዞን እንሰትን በስፋት በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
በዞኑ በተያዘው ዓመት 57 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኝ ተከላ መከናወኑ ተመላክቷል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ተክል ተሸፍኗል።
ዘንድሮም ልማቱን ለማስፋፋት ባለፋት ሁለት ወራት ከ57 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞች ተከላ መከናወኑን ተናግረዋል።
ከተክሉ የሚገኝ ዓመታዊ የምርት መጠንም ከነበረበት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉን አመልክተዋል።
ይህም ከተረጅነት በመላቀቅ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከማጠናከር ባለፈ ዞኑ የሚታወቅበትን የጥምር ግብርና ባህልን ለማዳበር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ልማቱን ለማስፋፋትና ለማዘመን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ በወረዳው ቡናና እንሰትን በዘመናዊ መንገድ በስብጥር በማልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የይርጋጨፌ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙ ተጠብቆ እንዲቆይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ የበልጉን ዝናብ በመጠቀም በ155 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ቡናና እንሰት በስብጥር መተከሉን አንስተው ይህም ዘመናዊ አሰራርን በማጠናከር ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሃይሌ ቦራ በበኩላቸው ባለፉት አመታት ከመንግስት ያገኙትን የእንሰት ችግኝ በዘመናዊ አሰራር በመስመር በማልማት በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለምርት መድረሱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የቆጮ ምርት ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
እንሰት በኩታ ገጠም በዘመናዊ መንገድ ከቡና ጋር በስብጥር ማልማታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ያነሱት ደግሞ በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ ማሞ ናቸው።