በዞኑ በዘጠኝ ወራት ከ41 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሀይል አማራጭ ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በዘጠኝ ወራት ከ41 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሀይል አማራጭ ተጠቃሚ ሆነዋል
ደሴ ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ41 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በተለያዩ የሀይል አማራጮች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ጽጌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የገጠሩን ማህበረሰብ በአማራጭ ሀይል ተጠቃሚ በማድረግ አኗኗሩን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የታዳሽ ሀይል ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ከ41ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የአማራጭ ሀይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ለዚህም ከ33 ሺህ 800 በላይ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን የማሰራጨት፣ 6ሺህ 947 በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ ሶላር ፓኔሎችን የማቅረብ እንዲሁም 311 ባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የመገንባት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በቀሪ ወራትም በግንባታ ላይ ያሉ 461 ባዮጋዞችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አማራጭ ሀይሉ ለምግብ ማብሰያና ለመብራት አገልግሎት ይጨፈጨፍ የነበረን ደን ከማዳን በተጨማሪ በጭስ ምክንያት በሴቶች ላይ ሲከሰት የነበረን የጤና ችግር ማቃለል ተችሏል ብለዋል።
አርሶ አደሩ በተመቻቸለት አማራጭ የሃይል አቅርቦት መጠቀሙ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪውን ከመቆጠብ ባለፈ ኑሮውን ለማሻሻልና ለማቅለል እንዳስቻለውም አስረድተዋል።
በተለይ የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርትን ለአፈር ማዳበሪያነት መጠቀሙ የማዳበሪያ ወጪን ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።
በተሁለደሬ ወረዳ የቀበሌ 08 ነዋሪ አርሶ አደር ያሲን አህመዴ በበኩላቸው፣ የተገነባላቸውን የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ምግብ ለማብሰልና ለመብራት አገልግሎት መጠቀም በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ለማገዶ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ከመቆጠብ ባለፈ ተረፈ ምርቱን ለማዳበሪያነት በመጠቀም የመሬት ለምነትና ምርታማነታቸውን ማሳደጋቸውን ጠቁመዋል።
የወረባቦ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ከድጃ ሰይድ በሰጡት አስተያየት፣ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ተጠቃሚ መሆናቸው ኑሯቸውን ማቃለሉን ተናግረዋል።
በተለይ በጭስ አማካኝነት ይፈጠር የነበረውን የጤና ችግር በማስቀረቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በተለያዩ የሀይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።