በያዝነው የመራጭነት ካርድ የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በያዝነው የመራጭነት ካርድ የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል
ሰቆጣ ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በመራጭነት ካርዳችን የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የምርጫ ካርድ በወቅቱ ማውጣታችን በቀጣይ አምስት ዓመት ሀገሪቱን የሚመሩ አካላትን ለመምረጥ ከወዲሁ እንድንዘጋጅ አድርጎናል።
የከተማዋ ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ልሳነ ወርቅ መንግስቴ " ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ሀገርን የሚያስተዳድሩ አካላትን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ አውጥቼ ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።
የመራጭነት ካርድ ለመያዝ ያሳዩትን ተነሳሽነትም በድምጽ መስጫው እለት ለመድገም በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወንም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሆነም ነው ያነሱት።
የመራጭነት ካርድ ማውጣታቸው በህገ- መንግስቱ የተቀመጠውን ዴሞክራሲያዊ መብት ለመጠቀም እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ሙሃባው ፈረደ ናቸው።
ባወጣሁት ካርድ ይበጀኛል ያልኩትን በመምረጥ የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣትና የምፈልገውን አካል ወደ ስልጣን ለማምጣት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ መብራት ውበቱ በበኩለቸው፤ ምርጫው አሳታፊና አካታች እንዲሆን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት እየታየባቸው ነው ብለዋል።
ማህበሩም ምርጫውን አስመልክቶ አስቀድሞ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመስራቱ አባላቱ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በማውጣት ለድምጽ መስጫው ቀን እንዲዘጋጁ አድርጓል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን ለማስተዋወቅ በመገናኛ ብዙሃን እያደረጉት ያለው የክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳም በእውቀት ላይ ተመስርቶ በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።