ቀጥታ፡

መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት ይሰራል

ወላይታ ሶዶ ፤ ሚያዝያ 23/2018(ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ገለጹ።

```ኃላፊው በወላይታ ሶዶ ከተማ ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ፕሮጀክቶችን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ የጀመራቸው የለውጥ ስራዎች የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ጠቅሰው የክልሉ መንግስትም ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡትና ትላንት ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች ብልፅግናን በተጨባጭ ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች ማሳያ መሆናቸውንም በምረቃው ላይ ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማሪያም በበኩላቸው የላሬና ኦሴ እና ጉትቶ ዱቡሻ ቀበሌ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቅ ለህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ከንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ባሻገር ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የድልድይ እና ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የህዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ፋንታ ኮርፖሬሽኑ አቅሙን አሳድጎ የውሃ ተቋማትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት ገንብቶ እያስረከበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ85 በመቶ በላይ እንደሚያደርሰው ገልጸው ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም የከተማውን ዕድገት በሚመጥን መልኩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በከተማው መርካቶ ክፍለ ከተማ የቦሳ ዚጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ባሳ ባራታ እና አቶ ኮርካ ኮሮቶ በአካባቢው የነበረው ድልድይ ተበላሽቶና በጎርፍ ተወስዶ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን ገልጸዋል።

የድልድዩ መገንባት ችግሩን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ በመሆኑ የከተማ አሰተዳደሩን አመስግነው ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥበቃ እንደሚያደርጉለትም ተናግረዋል።

የላሬና ኦሴ እና ጉቱቶ ዱቡሻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት  አቶ አበራ ጃጎ እና ታሪኩ ላአ በበኩላቸው በአካባቢው የንፁህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ የወንዝ ውሃ በመጠጣት ለበሽታ ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ ባደረገው ጥረትና ቁርጠኝነት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው የውሃ ተቋሙ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም