በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ለአህጉራዊ መሪነት መሰረት ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ለአህጉራዊ መሪነት መሰረት ሆነዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተመዘገቡ ስኬቶች ለኢትዮጵያ የዘርፉ አህጉራዊ መሪነት መሰረት መሆናቸውን የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው ተሹመዋል።
ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራርና ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ላለው የላቀ ሚና የተሰጠ እውቅና መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ሥነ-ምግባራዊ መርሆች በተከተለ መልኩ በማልማት፣ በመመራመር እንዲሁም ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን ለተሠሩ ሥራዎች እውቅና የሰጠ ነው ተብሏል።
የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአሠራር ሥርዓቷን ዲጂታል ለማድረግ እያከናወነች ያለችው ስራ በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
እንዲሁም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እንደ ትልቅ ተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን በስኬት የተጠናቀቀውን 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025' ስትራቴጂ እና በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' ስትራቴጂን በአብነት ጠቅሰዋል።
በተለይም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የአሰራር ቅልጥፍናን ለማምጣት እየተተገበረ ያለው የዲጂታል መንግሥታዊ አሠራር (e-government) ሥርዓት፣ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ እያከናወነች ያሉ ውጤታማ ሥራዎች እውቅና እያገኙ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፉን በአህጉር ደረጃ እንዲመሩ የሰጠው ሹመት የኢትዮጵያን ስኬትና አርዓያነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ያላቸውን ጥልቅ እውቀትና የዳበረ ልምድ መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ውጤታማ እንድትሆንና የለውጥ እርምጃዎችን እንድታፋጥን ቁልፍ የአመራርነት ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የዲጂታል ሥርዓት ግንባታ የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አርዓያ የሚሆንና አህጉራዊ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።