4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በመጪው እሁድ በይፋ ይከፈታል - ኢዜአ አማርኛ
4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በመጪው እሁድ በይፋ ይከፈታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ እሁድ ሚያዝያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ እንደሚከፈት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል አስታወቁ።
ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱና የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት መደረጉን አንስተዋል።
4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዝያ 25 እስከ 30 /2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልጸው፥ የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅና ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት የኤክስፖው ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠርና የምርት ጥራትን ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ፈጠራን ማበረታታትም አንዱ የኤክስፖው ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ መፍጠርም ዋነኛ ግቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤክስፖው 850 የንግድ ስምምነቶች እንደሚደረጉ ጠቅሰው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ150 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች እንደሚጎበኙት በመግለጫው ተብራርቷል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች፣ የምርት ልማት ውድድሮች፣ የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ፕሮግራም እና ሌሎችም መርሃ-ግብሮች እንደሚከናወኑ በመግለጫው ተመላክቷል።