በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው
ጂንካ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ ነው።
በክትባት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ እንዳሉት፤ በዘመቻው በክልሉ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ይከተባሉ።
ከክትባት ዘመቻው ጎን ለጎን በምግብ እጥረት የተገዱ ሕፃናትን የመለየትና የማከም ሥራ ይሰራል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሀ ያቆሩ ስፍራዎችን የማፋሰስ፣ አካባቢን የማፅዳትና በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።
የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በድሉ በጊማስ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ 5ኛ ዙር የፖሊዮ ክትባትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ቤት ለቤት በሚሰጠውና ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ የክትባት ዘመቻ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማው ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ቅድስት አብርሃም ከትባቱ ሕጻናትን ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል እንደሚያስችል ባገኙት ግንዛቤ መሰረት ልጃቸውን የፖሊዮ ክትባት እንዳስከተቡ ተናግረዋል።
ሌሎችም ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ በማስከተብ ጤናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የክትባት ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ታውቋል።