በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው
ጭሮ ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
በፅህፈት ቤቱ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቡድን መሪ አቶ ሳንዮ አደም ለኢዜአ እንደገለፁት ፤ በዞኑ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት የማስተዋወቅና የማልማት ስራ እየተካሔደ ነው።
መስህቦቹን ለቱሪዝም ልማቱ ከማዋል በተጨማሪ የአካባቢው ማሕበረሰብን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
እስካሁንም ከ50 በላይ መስህቦች በቱሪዝም መዳረሻነት ተለይተው በፅሑፍ የተሰነዱ ሲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም ስፍራዎቹን የማስተዋወቅና የማልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የኦዳ ቡልቱም አርዳ ጅላ እና የጨርጨር ሀይቅን ጨምሮ ጥንታዊ ዋሻዎች ያሉበትን አካባቢ ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ካሉ አስራ አንድ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ የሆነው የጨርጨር ሀይቅ የውሀ መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማገልገል እንዲችል እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በገዳ ስርዓት ከሚታወቁት አምስት ኦዳዎች አንዱ የሆነውን የኦዳ ቡልቱም አካባቢን ከዚሁ ሀይቅ ጋር በመሰረተ ልማት በማገናኘት የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚ ለመሳብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የቦኬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሀመድዘይን ጀማል እንዳሉት በወረዳው ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው ጥንታዊ መስጂድን እና የጨርጨር ሀይቅ ጎብኚዎችን ለመሳብ እንዲውሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟላላቸው እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በተያዘው ዓመትም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ከዋናው መንገድ እስከ ጨርጨር ሀይቅ የሚወስደው መንገድ እየተገነባ መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢው ወጣቶች ሐይቁን በመጠበቅና በመንከባከብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግም የወረዳው አስተዳደር ከ20ሺ በላይ የዓሳ ጫጩት በሀይቁ ውስጥ እያረባ መሆኑን ገልፀዋል።