በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከ336 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከ336 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል ይለማል
ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ከ336 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመኸር የምርት ዘመን በሩዝ ልማት ላይ ለውጥ የማምጣት ግብ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል።
የሩዝ ልማቱን በኩታ ገጠም በማረስ፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የሚጠበቀውን ምርት መሰብሰብ የሚያስችሉ ተግባራት ከወዲሁ መጀመራቸውን ገልፀዋል።
ከ336 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ በመሸፈን ከ18 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሩዝን ጨምሮ 10 ስትራቴጂካዊ ሰብሎች በልዩ ሁኔታ በክላስተር ለማልማት አቅጣጫ ተቀምጧል ያሉት አቶ ማንደፍሮ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር እቅዱን ለማሳካት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
የሩዝ ልማት በደቡብ ጎንደር ፎገራ ወረዳና አካባቢው ብቻ ተወስኖ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተስማሚ ስነ ምህዳርና የአየር ንብረት ባላቸው አብዛኛው የክልሉ ዞኖች እየተለመደ መምጣቱን ገልፀዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የቋር ሚካኤል ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አበራ ዘመናይ እንደገለጹት፣ ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ዝግጅት እያደረጉ ነው።
በዘርፉ ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ ቀድመው መውሰዳቸውን ጠቅሰው በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ለማግኘት እንደሚሰሩም አስረድተዋል።
ባለፈው የመኸር ምርት ዘመን በክልሉ በሩዝ ከለማው 208 ሺህ 636 ሄክታር መሬት ከ11 ነጥብ አምስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምረት መመረቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።