ቀጥታ፡

በከተማዋ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸው ተመላከተ።

በወላይታ ሶዶ ከተማ ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የወላይታ ሶዶ ከተማ የጀመራቸው የለውጥ ስራዎች የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ተገንብተው የተመረቁ ፕሮጀክቶች ብልፅግናን በተጨባጭ ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች ማሳያ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ 

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማሪያም በበኩላቸው የላሬና ኦሴ እና ጉትቶ ዱቡሻ ቀበሌ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቅ ለህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ፕሮጀክቱ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ከንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ባሻገር  ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የድልድይ እና ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የህዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ፋንታ ኮርፖሬሽኑ አቅሙን አሳድጎ የውሃ ተቋማትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት ገንብቶ እያስረከበ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ፕሮጀክቱ የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ85 በመቶ በላይ እንደሚያደርሰው ገልጸው ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም የከተማውን ዕድገት በሚመጥን መልኩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በከተማው መርካቶ ክፍለ ከተማ የቦሳ ዚጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ባሳ ባራታ እና አቶ ኮርካ ኮሮቶ በአካባቢው የነበረው ድልድይ ተበላሽቶና በጎርፍ ተወስዶ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን ገልጸዋል።


 

የድልድዩ መገንባት ችግሩን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ በመሆኑ የከተማ አሰተዳደሩን አመስግነው ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥበቃ እንደሚያደርጉለትም ተናግረዋል።

የላሬና ኦሴ እና ጉቱቶ ዱቡሻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት  አቶ አበራ ጃጎ እና ታሪኩ ላአ በበኩላቸው በአካባቢው የንፁህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ የወንዝ ውሃ በመጠጣት ለበሽታ ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ ባደረገው ጥረትና ቁርጠኝነት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው የውሃ ተቋሙ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም