ከኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ባገኘነው እውቀት የተቋማትን አሠራር የሚያዘምን ቴክኖሎጂ እየፈጠርን ነው-ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ባገኘነው እውቀት የተቋማትን አሠራር የሚያዘምን ቴክኖሎጂ እየፈጠርን ነው-ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ከአምስት ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ያገኙት እውቀትና ክህሎት የተቋማትን አሠራር የሚያዘምን ዲጂታል ሥርዓትና ቴክኖሎጂ እንዲፈጥሩ እንዳስቻላቸው የመዲናዋ ወጣቶች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የተቋማትን አገልግሎት የሚያሳልጥ የዲጂታል ሥርዓት ማበልፀግ የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት እንዳስቻለ ገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም የተጀመረው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና በርካታ ዜጎችን የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት ባለቤት እያደረገ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቩን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ኢትዮጵያን የሚያለሙ ዜጎችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
ወጣቶችም በመርሃ ግብሩ በመመዝገብ ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማበልፀግ የዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ባለቤት መሆን የሚችሉበትን ዕድል እንዲጠቀሙበት ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ ዜጎች በድረ-ገጽ ማበልጸግ፣ በአንድሮይድ መተግበሪያዎች ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ራሳቸውን እያበቁ ይገኛሉ።
ሰልጣኞቹም ሀገር በቀል መፍትሔዎችን በማፍለቅ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካ ጭምር የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቁ የፈጠራ ሥራዎችን እያበለጸጉ ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ስልጠናውን የወሰዱ ወጣቶች እንዳሉት፤ የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ችግር ፈቺ የዲጂታል ሥርዓቶችን ማበልፀግ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ወጣት ጌታሰው አበበ፤ ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ በ2010 ዓ.ም በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቆ በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በአይሲቲ ባለሙያነት እያገለገለ ይገኛል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና አራቱንም ስልጠናዎች በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የአንድሮይድ መተግበሪያ ማበልፀግ የሚያስችል ክህሎት ማግኘቱን ገልጿል።
በስልጠናው ያገኘውን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ያበለፀጋቸው ዘጠኝ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዕውቅና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግሯል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ.ም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተመረቀው ወጣት አዝመራው ታደሰ በበኩሉ፤ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት አስገኝቶልኛል ብሏል።
በስልጠናውም የቴክኖሎጂ ክህሎትን በማዳበር የአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞችን የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የሚያሳይ "አዲስ አበባ ኮደርስ" የሚል የዲጂታል ሥርዓት ማበልፀግ እንደቻለ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን( ዶ/ር)፤ የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና በዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የበለፀገ ዜጋ ማፍራት እያስቻለ ነው ብለዋል።
ስልጠናውን የወሰዱ የከተማዋ ወጣቶችም የዘመናዊነትና ምክንያታዊነት ዕሳቤን በማዳበር የተቋማትን አገልግሎት የሚያሳልጥ የዲጂታል ሥርዓቶችን እያበለፀጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ከ809 ሺህ በላይ ዜጎችን ለማሰልጠን ታቅዶ፥ ከ900 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የተመዘገቡ ሲሆን 678 ሺህ የሚሆኑት ስልጠናውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
በአራቱም የኢትዮ ኮደርስ የዲጂታል ክህሎት ልማት አማራጮች ብቃት ያላቸውን ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።