የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ በሊድስ ዩናይትድ እና በርንሌይ መካከል ይካሄዳል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ በኢላንድ ሮድ ፓርክ ስታዲየም ይደረጋል።
ሊድስ ዩናይትድ በ40 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ከሊጉ መውረዱ የተረጋገጠው በርንሌይ በ20 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ መድረክ ለስምንተኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን፣ በታሪክ ሊድስ ዩናይትድ የበላይነቱን ይዟል።
ቀደም ሲል ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ሊድስ አምስት ጊዜ ድል ሲቀናው፣ በርንሌይ በአንድ ጨዋታ ብቻ አሸንፎ በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በሰባቱ ጨዋታዎች ላይ ሊድስ ዩናይትድ 15 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በርንሌይ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል።
ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የውድድር ዓመት በስምንተኛው ሳምንት ተገናኝተው በርንሌይ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ይህም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪኩ በሊድስ ላይ ያገኘው ብቸኛ ድል ነው።
ሊድስ ዩናይትድ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ መራቅ የሚያስችለውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።
ለበርንሌይ ጨዋታው ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ትርጉም የለውም።
የዛሬውን ጨዋታ የ36 ዓመቱ ቶም ብራሞል በዋና ዳኝነት እንዲመሩት ተመድበዋል።
የ35ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብርም እስከ መጪው ሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።