ቀጥታ፡

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።

ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት ስቧል።

በሊጉ ካደረጋቸው 28 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11ዱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

በ28ቱ ጨዋታዎች ላይ 24 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 27 ጎሎች  ተቆጥረውበታል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ35 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሊጉ 28 ጨዋታዎችን አከናውኖ 15 ጊዜ ድል ሲቀናው በአራቱ ተሸንፏል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 35 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 17 ጎሎች ተቆጥሮበታል።

ሲዳማ ቡና በ54 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ከቀናት በፊት በ20ኛ ሳምንት የሊጉ ተስተካካይ መርሐ ግብር 3 ለ 1 የተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ድል የቀናው ሲዳማ ቡና ማሸነፍ መሪነቱን እንዲያጠናክር ያስችለዋል።

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከምድረ ገነት ሽሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ በ36 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ምድረ ገነት ሽሬ በ29 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በዘንድሮው ዓመት በሊጉ በርካታ ጨዋታዎች (15 ጊዜ) አቻ የወጣው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት ሁለት መርሐ ግብሮች ድል አልቀናውም።

ምድረ ገነት ሽሬ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከድል በመራቅ የውጤት ማጣት ቀውስ ይገኛል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይፋለማሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እያደረገ ባለው ፉክክር ሶስት ነጥብ እጅጉን ያስፈልገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም