ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ቡናን 4 ለ 2 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጋናዊው ኮንኮኒ ሃፊዝ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ያሬድ ከበደና በየነ ባንጃ ቀሪዎቹን ጎሎች ለወልዋሎ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አቡበከር አዳሙ እና በረከት ብርሃኑ ለኢትዮጵያ ቡና ጎሎችን አስቆጥረዋል።
በሊጉ ስምንተኛ ድሉን ያገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ35 ነጥብ ካለበት 17ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና በ41 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና እና መቀሌ 70 እንደርታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ነገሌ አርሲ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።