የምግብና ስርዓተ ምግብ ትግበራን ማጠናከር ለህጻናትና እናቶች ጤና መሻሻል ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምግብና ስርዓተ ምግብ ትግበራን ማጠናከር ለህጻናትና እናቶች ጤና መሻሻል ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-የምግብና ስርዓተ ምግብ ትግበራን ማጠናከር ለህጻናትና እናቶች ጤና መሻሻል ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር መካከለኛ የምግብ አለመመጣጠን ህክምናን በሚመለከት ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ የመካከለኛ የምግብ አለመመጣጠንን በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብርና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ሥርዓት ውስጥ በማካተት ማከም እንደሚቻል አመላክቷል።
ሂደቱም አስፈላጊ የሆኑ የስርዓተ ምግብ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚ ህጻናት እና ቤተሰቦች በማቅረብ የሚከናወን ነው ተብሏል።
ይህም ኢትዮጵያ ህጻናትን፤ ነፍሰ ጡር ሴቶችን እና የሚያጠቡ እናቶችን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ተገልጿል።
በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ህይወት ዳርሰኒ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶችን የስርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታለች።
ጥናቱ ትኩረት የሚሹ ቁልፍ ችግሮችን በመለየት የመካከለኛ የምግብ አለመመጣጠንን በመደበኛ የመጀመሪያ ጤና ክብካቤ ስርዓት በማካተት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ለትግበራውም ዘላቂ የሆነ ፋይናንስ፣ ጠንካራ የአቅርቦት ስርዓት እና ለጤና ባለሙያዎች ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናን በመስጠት በኩል ሚኒስቴሩ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል አርጋው በበኩላቸው፤ የጋራ ጥናቱ በምርምር ላይ የተደገፈ የጤና ስርዓትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት፣ በህጻናትና እናቶች የመካከለኛ የምግብ አለመመጣጠን ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ አጋዥ ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።