ቀጥታ፡

ስፖርት ለሰላም ግንባታና ለህዝብ ትስስር መጠናከር ያለውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት ይሰራል

ጂንካ፤ ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ)፦ ስፖርት ለሰላም ግንባታና ለህዝብ ትስስር መጠናከር ያለውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለጸ።

3ኛ ዙር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ በጂንካ ከተማ ተጀምሯል።

በመክፈቻ ሥነ-ስርአቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደመላሽ ይትባረክ እንዳሉት፣ የሻምፒዮና ውድድሩ በክልሉ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚካሄደው ነው።

ሻምፒዮናው ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ የባህል ልውውጥ ለማድረግ እና የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በመሆኑም ስፖርታዊ ውድድሮች ከመዝናኛነት ባሻገር ለሰላም እሴት ግንባታና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሳይ ጋልሺ በበኩላቸው የክለቦች ሻምፒዮናው ለ15 ቀናት የሚካሄድ ነው ብለዋል።

በውድድሩም በክልሉ የሚገኙ 18 የወንዶች የእግር ኳስ ክለቦች እና 5 የሴቶች የእግር ኳስ ክለቦች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 4ኛ የወጡ ክለቦች በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒና ላይ ክልሉን ወክለው ይሳተፋሉ ብለዋል።

ክልሉ የብዝሀ ባህልና እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች መገኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስፖርታዊ ውድድሮች እነዚህን ሀብቶችን ጭምር ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና አላቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም