ቀጥታ፡

ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም የድምጽ መስጫ ዕለትን እየተጠባበቅን ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርዳቸውን በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዕጩዎቻቸውን ከማስመዝገብ ባለፈ ማኒፌስቶዎቻቸውን በማስተዋወቅና የቅስቀሳ ዘመቻዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት፤ ምርጫ ለአንድ አገር የዴሞክራሲ ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለልማት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው።

ወይዘሮ ትዕግሥት ጸጋዬ በሰጡት አስተያየት፤ ለምርጫው ሰላማዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሐዊነት የሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ዜጎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ካርዳቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡ 

ለሕዝብና ለአገር ይበጃል የሚሉትን ለመምረጥ የምርጫ ካርዳቸውን ወስደው ቀኑን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል። 

አቶ ታሪኩ ዘላለም በበኩላቸው ምርጫ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉበትና የመፃኢ እድላቸውን የሚወስኑበት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የምርጫ ካርዳቸውን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው ለሕዝብና ለአገር ይበጃል የሚሉትን ለመምረጥ ቀኑን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል። 

"የአንድ ሰው ድምፅ ትልቅ ዋጋ አለው፤ ያንን ዋጋ ያለው ድምፅ ደግሞ በአግባቡ ለመጠቀምና የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ካርዴን ይዤ ቀኑን እየጠበቅኩ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ሲሳይ ጉታ ናቸው። 

የምርጫ ካርድ መውሰድ ብቻውን በቂ አለመሆኑንና ይጠቅመናል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ መስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። 

በተመሳሳይም አቶ መልካሙ ኩመራ እና ወይዘሪት እናትነሽ ፍሥሐ፤ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ቀድመው ካርዳቸውን መውሰዳቸውን አስታውሰው፣ አሁን ላይ የቀራቸው ብቸኛ ተግባር በዕለቱ ተገኝተው ድምፅ መስጠት መሆኑን ተናግረዋል። 

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሚለካው በዜጎች ንቁ ተሳትፎ በመሆኑ፣ ሁሉም መራጭ ካርዱን ይዞ በዕለቱ እንዲገኝና ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም