የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡለትን የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መራ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡለትን የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መራ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ) ፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀረቡለትን የተለያዩ ረቀቂ አዋጆች መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅትም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላትን ሹመት በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን፣ አንጎላ፣ ባንግላዲሽ እና ኢስዋቲኒ ጋር ያደረገችውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ አራት ረቂቅ አዋጆች መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያና ሩሲያ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈራረሙትን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበን ረቂቅ አዋጅ በመመርመር ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
እንዲሁም በኢትዮጵያና ቬትናም መካከል የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር)፤ ከሀገራቱ ጋር የተፈረሙት የአየር አገልግሎት ስምምነቶች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
ከቬትናም ጋር የተደረገው የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ቪዛን የማስቀረት ስምምነትም የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከሩሲያ ጋር የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመው ስምምነት ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር የትብብር ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላትን ሹመት መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ተሿሚዎቹ በትምህርት ዝግጅት እንዲሁም ባዳበሩት ክህሎት የድርጅቱን ተልዕኮ ማሳካት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመመርመር ብሌን ማሞን በቦርድ ሰብሳቢነት በመሰየም፤ ፈዲላ ቢያ፣ ተስፋዬ ዘውዴ፣ መሐመድ ካሳ፣ አፈወርቅ በደዊ፣ አስማ ረዲ፣ ዮናስ በቀለ፣ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር እና ኢሳያስ ካሳን (ዶ/ር) በቦርድ አባልነት በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
የድርጀቱ የቦርድ ተሿሚዎችም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።