ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ በተመቻቸላቸው ዕድል የመራጭነት ካርድ እየወሰዱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ በተመቻቸላቸው ዕድል መሠረት የመራጭነት ካርዳቸውን እየወሰዱ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ያከናወነ ሲሆን፤ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት ጠቅላላ ምርጫም መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊዮን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችለቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል።

በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ድምፅ መስጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርስቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ የመራጮች ምዝገባን አራዝሟል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ተጨማሪ የምዝገባ ጊዜ በመጠቀም የምርጫ ካርድ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ ሳሙኤል ኢሳያስ፤ የአንድ ሀገር ምርጫ የዜጎችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ የሚወስን የጋራ መድረክ ነው ብሏል።

በዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ደምፅ መስጠት የሚችልበትን የምርጫ ካርድ በማውጣት ይበጀኛል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት ተማሪ አበበ አብዮት በበኩሉ፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ባህል መገንቢያና የዜጎችን የስልጣን ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ተናግሯል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ አቅርቧል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱን አንስቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ ኤልሻዳይ በለጠ፤ ምርጫ የዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግስታዊ የመምረጥ መመረጥ መብት መጠቀሚያ መሳሪያ መሆኑን ገልጻለች።

በዚህም ምርጫ ቦርድ የሰጠውን የልዩ ምዝገባ ተጨማሪ ጊዜ በመጠቀም ምርጫ ካርድ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኗን አስረድታለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የተሻለ ሀሳብ የያዘ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን የተናገረው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪ ለሚ መንግስት ነው።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካልና ኮምፒተር ኢንጅነሪንግ ተማሪ ሰለሞን ታረቀኝ፤ ተጨማሪ ጊዜያትን በመጠቀም የምርጫ ካርድ እንደሚወስድ ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው ሌላኛው ተማሪ ብሩክ ጣዕም በበኩሉ በዲጂታል የምርጫዬ አማራጭ ምርጫ ካርድ በመውሰድ ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረጉን ተናግሯል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም