በክልሉ የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ነው
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ መምሩ ሞኬ፤ በክልሉ የግብርና ልማት እንቅስቃሴንና የተገኙ ውጤቶችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም ከሰባት በላይ አዳዲስ የግብርና ልማት ኢንሸቲቮች ተቀርጸው በሥራ ላይ በማዋል የምርት አማራጭንና ምርታማነትን የማሳደግና የሥራ ዕድልን የማስፋት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለመስኖ ልማት በተሰጠው ትኩረት በትናንሽ የውሃ አማራጮች፣ ከ28 በሚበልጡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ አውታሮች ሰፊ መሬት ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በተያዘው ዓመት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር በማልማት ከ22 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ለሥራ ልድል ፈጠራም ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመስኖ ልማቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው የሰብል ልማትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምርቱ ከ384 የሸማች ማበራት ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱ የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻሉ በላይ ገበያን በማረጋጋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አክለዋል።