በዞኑ በመጪው ክረምት በ884 ሔክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል ችግኝ ይተከላል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመጪው ክረምት በ884 ሔክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል ችግኝ ይተከላል
መቱ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በኢሉአባቦር ዞን በመጪው ክረምት በ884 ሔክታር መሬት ላይ 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ህብረተሰቡ ከሌሎች የግብርና ስራዎች ጎን ለጎን በሻይ ልማት ኢንሼቲቭ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም ዘንድሮ በ884 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል ችግኞችን ለማልማት ታቅዶ የችግኝና የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ስራ በሰፊው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው ዓመትም 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞችን ማዘጋጀት እንደተቻለ የተናገሩት ኃላፊው፣ ከዚህም ውስጥ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞች በመጪው ክረምት በ884 ሔክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉ ገልፀዋል።
የልማት ስራው በዞኑ ስድስት ወረዳዎች በሚገኙ 22 ቀበሌዎች እየተከናወነ ሲሆን፣ አርሶ አደሮችና የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን ጨምሮ ከ400 በላይ ዜጎች በልማቱ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ በሻይ ልማት ግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶአደሮችም የሻይ ልማት ስራ በሁሉም ደረጃ በአብዛኛው በሰው ኃይል የሚሰራ በመሆኑ ለበርካቶች የስራ ዕድልን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ለምርት ደረጃ ሲደርስ በየሁለት ሳምንቱ እየተለቀመ ለፋብሪካ የሚቀርብ በመሆኑ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ለሌሎች የስራ እድሎችን እየፈጠሩ ለራሳቸውም ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውንም ነው አርሶአደሮቹ የገለጹት።