ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማ ማሳ ከ44 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ 

አርባ ምንጭ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በጋሞ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 1ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከ44 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በ13 የዞኑ ወረዳዎች 1ሺህ 380 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል።

ከልማቱም ከ44 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንና የምርታማነት መጠንም በሄክታር በአማካይ 32 ኩንታል መድረሱን ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም መከናወኑን አስታውሰው፣ ለልማቱ በአጠቃላይ 2ሺህ 760 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ዩሪያ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

በምዕራብ አባያ ወረዳ የሳውዝ አግሪ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ከበደ፣ ድርጅቱ በ20 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማከናወኑን ገልጸው፣ ምርታማነትም በሄክታር 35 ኩንታል ደርሷል ብለዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተገኘ ያለው ምርት የአካባቢው አርሶ አደሮችን በማነቃቃት በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ባይለመድም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በልማቱ በመሳተፍ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ በቁጫ ወረዳ የፋንጎ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ሚሊዮን በየነ ናቸው።

ዘንድሮ በበጋ ወቅት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ካለሙት ስንዴ 66 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በልማቱ የሚያገኙት ምርት የቤት ውስጥ ፍጆታቸውን ከመሸፈን ባለፈ ገቢያቸውን ለማሳደግ እያገዛቸው መሆኑንም ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም