ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዐቅም እንዲጎለብት አድርጓል 

ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማነቃቃት የማምረት ዐቅም እንዲጎለብት ማድረጉን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሠ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

"ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" በሚል  መሪ ሐሳብ የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።



 
አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማነቃቃት የማምረት ዐቅም እንዲያድግ አስችሏል።
 
መንግሥትንና ባለሃብቱን በማቀራረብ ችግሮችን በጋራ በመፍታት፣ ተሞክሮ በመለዋወጥ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥራን በማጠናከር ለአምራች ኢንዱስትሪው እድገት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አስረድተዋል።

ቆመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ማነቆ በመፍታት ጭምር ተኪና ለውጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ኢኮኖሚያዊ እድገቱ እንዲፋጠን አስችሏል ሲሉም አክለዋል።
 
በክልሉ ዝቅተኛ የነበረውን የኢንዱስትሪዎች የማምረት ዐቅም አሁን ላይ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ የደብረ ብርሃን ከተማም ለኢንዱስትሪ ልማት ተመራጭ እንድትሆን አግዟል ብለዋል።



 
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ “በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ታግዞ እየተካሄደ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ልማት በበጀት ዓመቱ ሥራ አቁመው የቆዩ 46 መካከለኛና አነስተኛ እንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ አስችሏል ብለዋል።



 
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ደግሞ፤ ወደ አካባቢው መጥተው ማልማት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ  ትኩረት መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም