እንቁላል ሳይበላሽ ለሁለት ዓመት እንዲቆይ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለሕብረተሰቡ እየተዋወቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
እንቁላል ሳይበላሽ ለሁለት ዓመት እንዲቆይ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለሕብረተሰቡ እየተዋወቀ ነው
ጎንደር፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዶሮ እንቁላል ሳይበላሽ ለሁለት ዓመት ያህል ማቆየት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ወደ ተግባር ለማስገባት ለዶሮ ዕርባታ፣ ለአርሶ አደሮችና ለግለሰቦች ተግባር ተኮር ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ማስተዋል ብርሃን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የእንቁላል ምርት ብክነትና ብልሽትን ለማስቀረት ሲሠራ ቆይቷል።
በዚህም እንቁላልን እስከ ሁለት ዓመት ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችል ቴክኖሎጂን የማላመድና የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው በአንድ ሊትር ውኃ ውስጥ 30 ግራም የኖራ አፈር ወይም ላይም ስቶን ጨምሮ በማዋሃድ እስከ 12 እንቁላሎችን ሳይበላሽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ ተመራጭ ነው ብለዋል።
በተለይም በጾም ወራት የእንቁላል ምርት ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በማቆየት በፍስክ ወቅት ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑ ለሀገራችን ተመራጭ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የኖራ አፈር ወይም ላይም ስቶን እንቁላል ቶሎ እንዳይበላሽ የሚያግዝ ካልሽየም ካርቦኔት የተባለ ውህድ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የዶሮ እንቁላሎቹ ወደ ተዘጋጀው ማቆያ ከመግባታቸው በፊት በቅድሚያ ንጹህና ምንም አይነት ቆሻሻና ርጥበት በላያቸው ላይ አለመኖሩን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስረድተዋል።
እንደ አካባቢው የአየር ሁኔታ አንድ እንቁላል ሳይበላሽ መቆየት የሚችለው እስከ ሁለት ሳምንት መሆኑን ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂው ይህን ችግር በመሰረታዊነት የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂውን በስፋት በማስተዋወቅና በማላመድ ረገድም ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን በመስጠት ችግር ፈቺነቱን የማሳየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቴክኖሎጂው የሀገሪቱን የእንቁላል ብክነት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር አንማው እሸቴ ናቸው፡።
ያደጉት ሀገራት ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙበት የቆዩና ውጤታማነቱ በተግባር ተፈትሾ የተረጋገጠ ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸው፤ ለሀገራችን ዶሮ አርቢዎች አዲስና አዋጭ መሆኑን ጠቁመዋል።