ቀጥታ፡

በፋይናንስ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ውስን የሆነውን የመንግሥት ሀብት ከብክነት ታድጓል

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በፋይናንስ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ውስን የሆነውን የመንግሥት ሀብት ከብክነት ለመታደግ ማስቻሉን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ።
 
ቢሮው "ውጤታማ የፋይናንስ አሥተዳደር ለክልላችን ሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ነው።
 
በምክትል ርዕሠ መሥተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በክልሉ በፋይናንስ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ውስን የሆነውን የመንግሥት ሀብት ከብክነት ለመታደግ አስችሏል።
 
በዚህም ያለፉትን ዘጠኝ ወራት ጨምሮ በ2 ዓመት ተኩል ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች 50 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 536 ፕሮጀክቶች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
 
ይህም በክልሉ ውጤታማ የፋይናንስ አሥተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት በተከናወኑ ሥራዎች የመጣ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። 
 
የክልሉ መንግሥት በ2018 በጀት ዓመት ከ62 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል በምክር ቤት አጸድቆ በመደበኛና በካፒታል ለይቶ በመደልደል ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፤ በዚህም ተስፋ ስጪ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።

የመንግሥትን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም የዘርፉ አመራሮች እና የሴክተር መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስ አሠራር ሥርዓቱን መቆጣጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም