ባሕር ዳር ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባሕር ዳር ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው
ባሕር ዳር፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- የባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ገለጹ።
የከተማ አሥተዳደሩ የዘጠኝ ወራት የመንግሥትና የፓርቲ የሥራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በባሕር ዳር መካሔድ ተጀምሯል።
ምክትል ከንቲባው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የከተማዋን ገፅታ በተሻለ ደረጃ መቀየር የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ ባለፈ፤ ማራኪ፣ ለነዋሪዎች ብሎም ለጎብኝዎችና ለኢንቨስትመንት የተመቸች በማድረግ በኩል የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
ሕዝቡንና ባለሃብቱን በማሳተፍ የመዝናኛ ቦታዎችን በመገንባት፤ የአረንጓዴ እና የፓርክ ልማት ሥራዎች ተጨማሪ ገቢና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከልን ወደ ሥራ በማስገባት 72 አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ አግባብ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብና፣ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጠንካራ ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለም አስረድተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የከተማውን ሕዝብና ወጣት በማሳተፍ በተሠራው የሰላም ማስከበር ሥራ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደተቻለ ገልፀዋል።
ይህን ተከትሎም የልማት ሥራዎችን ያለምንም ስጋት ማከናወን የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ በሆነ አግባብ እንዲካሄድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያካተተ ምክር ቤት ተቋቁሞ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደተቻለም አንስተዋል።
በቀጣይም የምርጫ ሥራዎችን ጨምሮ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ሕዝብን ባሳተፈ አግባብ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።