የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ገፅታ በማጉላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ገፅታ በማጉላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር ያስችላል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ገፅታ በማጉላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚረዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ተናገሩ።
የኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ቱባ ባህል፣ ውብ ተፈጥሮ፣ የከተማ ልማትና የእንግዳ ተቀባይነት ባህላዊ ዕሴት የሚያሳይ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የሮማንያ ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀው 2ኛ የዲፕሎማቲክ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ አያት ሪጀንሲ ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
"አፍሪካ በዲፕሎማት ዕይታ" በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት እ.አ.አ ትናንት ሚያዚያ 29/2026 የተከፈተ ሲሆን በፈረንጆቹ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2026 ድረስ ይቆያል።
በመክፈቻ ዝግጅቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የሮማኒያ ኤምባሲ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገራት አምባሳደሮችና ተጋባዥ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ አዲስ አበባ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማቲክ ማዕከል የሆነች መዲና ናት ብለዋል።
የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራትን ቱባ ባህልና የተፈጥሮ ፀጋ በማስተዋወቅ ለገፅታ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም የፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንኙነትን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብና የባህል ልውውጥን የበለጠ ለማዳበር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለይም የኢትዮጵያን እውነተኛና ትክክለኛ ገፅታ በመግለጥና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ ዘርፉን የበለጠ ለማናቃት ከፍተኛ አስተዋጸኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ነብዩ ተድላ በበኩላቸው፤ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ዝግጅቱም የኢትዮጵያን የመስህብ ስፍራዎች በማስተዋወቅና የዜጎችን የባህል ብዝኅነትና ውብ ፀጋዎች በመግለጥ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓቲካ በበኩላቸው፤ ዝግጅቱ ዲፕሎማቶች ከሚያደርጓቸው የፖለቲካል ኢኮኖሚክ ግንኙነትን ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።
የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በቀጣይም ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።