ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ80 ዓመታት ጉዞ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር አህጉራዊ ምልክትነቱን እያስቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ80 ዓመታት ጉዞ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር አህጉራዊ ምልክትነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ የአየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት ከደንበኞችና አጋሮች ጋር የደንበኞች ተሞክሮ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ አየር መንገዱ ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት የዕድገትና ስኬት ጉዞዎችን በማድረግ ዛሬ ያለበት ደረጃ ደርሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካይሮ አንድ ብሎ በረራ የጀመረውን የዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት አሁን ላይ መዳረሻውን ወደ 145 ማስፋቱን ተናግረዋል።

በዚህም 147 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በዓመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞች ማስተናገድ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም መገንባቱንም ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ለደንበኞች ምስጉን አገልግሎት በመስጠት ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ሽልማት ማግኘት መቻሉንና ለመላው አፍሪካ ሞዴል የሆነ ግዙፍ አየር ማረፊያ እየገነባ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባለፉት 80 ዓመታት በርካታ ፈታኝ ወቅቶችን በስኬት በማለፍ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ እንድትሆን በማስቻል አህጉራዊ ምልክትነቱን እየስቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታትም 74 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ማምጣቱንና 117 አውሮፕላኖችን ማዘዙንም አብራርተዋል።

በዚህም የመንገደኞችን ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ ዓመታዊ ገቢውን 120 በመቶ እንዲሁም ትርፉንም በሦስት እጥፍ ማሳደጉን አንስተዋል።

Ethiopian News Agency #ኢዜአ #የኢትዮጵያ_አየር_መንገድ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም