ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እያከናወነች ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እያከናወነች ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተፈላጊነቷን የሚያሳድግና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።
አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ ባለፉት ሳምንታት የቡሩንዲ፣ ላይቬሪያ፣ ሞዛምቢክና ደቡብ ሱዳን መሪዎች በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን አውስተዋል።
መሪዎች በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች ከፍተኛ ዕድገት ባስመዘገበችባቸው ዘርፎች ላይ ልምዷን ለማካፈልና በትብብር ለመስራት የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረሟንም ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ የፖርቹጋል፣ የባንግላዲሽና ኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የምታራምደውን አቋም በሚገባ ያንፀባረቀችበት መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በስዊድንና ኖርዌይ ባደረጉት ጉብኝት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ ከኩባንያ አመራሮች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት በተለይ በታዳሽ ኃይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላትን ዲፕሎማሲያዊ ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷን በሚገባ እየተወጣች መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ አፍሪካ የሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይ ምክክር እንዲደረግበት አጀንዳ ማቅረቧን ጠቅሰው፤ በሌሎች አሕጉራዊ የሰላምና ደሕንነት ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቧን ማጋራቷንም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተግባራት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀባይነቷን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።