የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት የሚበጅ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት የሚበጅ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናገሩ
ደሴ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት የሚበጅ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን በጉጉት እየጠበቅን ነው ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
አቶ ፀጋዬ ረታ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ይበጃል ለምለው ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ዕለቱን በጉጉት እየጠበኩ ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ማንን መምረጥ እንዳለብን ግንዛቤ የፈጠረ በመሆኑ፤ በምርጫው ለሀገር እድገት የሚበጅ አካል ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።
ወይዘሮ ምሳ ኡመር እንደገለጹት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና አብሮነት ይጠቅማል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ።
ለዚህም ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ የምርጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ ዘላቂ ሰላም መኖር ያለበት በመሆኑ ሰላማችንን እየጠበቅን ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለንም ብለዋል።
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመመስረት ምርጫ ወሳኝ በመሆኑ የምርጫ ካርድ በማውጣት የሚጠበቅብኝን ተሳትፎ ለማድረግ እየጠበኩ እገኛለሁ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እታፈራሁ ከበደ ናቸው።
ሁላችንም የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ አለብን፤ የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣትም መዘጋጀት ያስፈልገናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሊያሳድግ ይችላል የምለውን ፖርቲ በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቴን እጠቀምበታለሁም ነው ያሉት።