ሀገራዊ ለውጡ የክልሉን ግብርና በማዘመን ወደ ላቀ የምርታማነት ምዕራፍ አሸጋግሯል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ የክልሉን ግብርና በማዘመን ወደ ላቀ የምርታማነት ምዕራፍ አሸጋግሯል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግብርናው በቴክኖሎጂ የሚደገፍበት አሰራር መዘርጋቱ የክልሉን ምርትና ምርታማነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለፁ።
ከለውጡ በፊት በክልሉ ዓመታዊ የምርት መጠን 18 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን፥ አሁን ወደ 60 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማደጉን አብራርተዋል።
መንግሥት ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ብዝኃ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ግብርና አንዱ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም የባለ አነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን የኩታ ገጠም እርሻ፣ የሜካናይዜሽን እና የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ከፍተኛ እመርታ መጥቷል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን ራስን በምግብ የመቻል ግብ እንዲሳካ፣ በክልሉ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የግብርና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በክልሉ ከራስ ፍጆታ ባለፈ በስፋት ለገበያ በማቅረብ ረገድ ትልቅ አቅም ወደሚፈጥር የምርታማነት ምዕራፍ ሽግግር እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከለውጡ በፊት በክልሉ ዓመታዊ የምርት መጠን 18 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን፥ አሁን ወደ 60 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉን አብራርተዋል።
እነዚህ ውጤቶች ሊመዘገቡ የቻሉት በክልሉ የሚከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎች በልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎች እንዲደገፉ ትኩረት አድርጎ በመሠራቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ባለሀብቶች እንዲሠማሩ ከማድረግ ባለፈ አርሶ አደሮች በዘርፉ በዘመናዊ መልኩ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም ለተመዘገበው ውጤት መነሻ ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ አያይዘውም የተቀናጀ የግብርና ልማት የተለያዩ የግብርና ምርት አይነቶችን በአንድ አካባቢ ማምረት የሚቻልበትን አቅም የሚያጎለብት በመሆኑ የኸልዋ አግሮ ኢንዱስትሪን በማቋቋም ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በኢንዱስትሪው እየተመረቱ ካሉ ምርቶች መካከል አትክልትና ፍራፍሬ እና የተለያዩ የእንስሳት ተዋጽኦዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው በተቀናጀ የግብርና ስራ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ባለሀብቶች፣ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ልምድና ተሞክሮ ቀስመው የተሻለ ስራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሆሞሻ ወረዳ የተቀናጀ የእርሻ ልማት ስራ ላይ የተሰማሩት ፍቃዱ ነመራ በበኩላቸው፥ በ2016 ዓ.ም በመስኩ ላይ እንደተሰማሩ ያወሳሉ።
በክልሉ ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ጸጋ እያለ የግብርና ምርቶችን ከመሸመት ይልቅ ለምን ማምረት አልጀምርም በሚል ቁጭት ወደ ግብርና ልማት እንደገቡ ገልጸዋል።
በተቀናጀ የግብርና ስራ የተለያዩ ቋሚ ተክሎችና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት በማምረት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በማምረት ላይ ከሚገኙት ቋሚ ተክሎች መካከል አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ብርቱካንና ሌሎችም የሚገኙበት ሲሆን የማር፣ የዶሮና የእንሥሣት ምርት ላይም ትኩረት መስጠታቸውን አብራርተዋል።
የሚመረቱ ምርቶችን ምርታማነት ለማሳደግ የከርሠ ምድር ውሃን በመጠቀም መስኖና የተፈጥሮ ማዳበሪያን እየተጠቀሙ ምሆኑን ገልፀዋል።
በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ክትትልና ድጋፎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ አቅም እየፈጠረላቸው እንደሚገኝም አንስተዋል።
ሁሉም ህብረተሰብ በየአካባቢው ያለውን እምቅ ጸጋ በትጋት ካለማ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የያዘችውን እቅድ እንደምታሳካ ጠቅሰው፥ ለዚህም የበኩላቸውን አሻራ በማሳረፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።