ቀጥታ፡

የአምቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መሻሻል ከእንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች

አምቦ፤ ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡- የአምቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መሻሻል ከእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ ታድጎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ገለጹ።


 

ሻምበል አንዷለም ገረመው በሰጡት አስተያየት፤ በማዘጋጃ ቤቱ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የቀናት ምልልስን በመጠየቁ ሳቢያ የጊዜ ብክነት ያጋጥም ነበር ብለዋል።
 
አሁን አገልግሎቱ የዘረጋው ፈጣን አሠራር ተደራጅተው መሬት ለመጠየቅ የመጡበትን ጉዳይ በፍጥነት ለማስፈጸም እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
 
የማዘጋጃ ቤቱ ቀልጣፋና ዘመናዊ ሂደትን የተከተለ አሠራር እንግልትን የቀረፈ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡



 
በማዘጋጃ ቤቱ የተጀመረው ዘመናዊ አገልግሎት የመጡበትን ካርታ የማውጣት ጉዳይ በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቁ እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ ወርቅነሽ ዴሬሳ ናቸው።


 

ያዴሳ ቡልቱማ በበኩላቸው በነባሩ አሠራር መረጃ ጠፋ በሚል ባለ ጉዳይን የማጉላላት ሁኔታ እንደ ነበር አውስተው፤ አሁን አገልግሎት አሰጣጡ በመሻሻሉ ጉዳያቸውን በፍጥነት ማስፈጸማቸውን አስረድተዋል።


 

ማዘጋጃ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ባለ ጉዳዮች በፍጥነት የሚስተናገዱበትን ሂደት ለማሳካት የሰው ኃይልና በግብዓት የማሟላት ሥራ መሠራቱን ያስታወቁት ደግሞ የአምቦ ከተማ አሥተዳደር ማዘጋጃ ቤት ምክትል ኃላፊ ሙሊሳ ፈዬራ ናቸው።

ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍና መልሶ በማደራጀት ቀደም ሲል አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ይወስድ የነበረን ምልልስ በማስቀረት ተገልጋዮች ባጠረ ጊዜ ጉዳያቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም