የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ ምኅዳር ፈጥሯል-አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ ምኅዳር ፈጥሯል-አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶች ምች ምኅዳርን ፈጥሯል።
የዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶችም የኢትዮጵያን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ በመጠቀም በተለያዩ የልማት መስኮች እንዲሰማሩ እያደረገ ይገኛል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያፋጥን ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድል ያላት ሀገር ናት።
የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንትን አማራጭ ለማስፋት መንግስት የሚወስዳቸው የፖሊሲ አማራጮችም የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ ልማትን ለማበረታታት የተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራትም ኢትዮጵያን አፍሪካዊት ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትጵያና ፈረንሳይ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማስፋትም በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ፈረንሳይም የሀገራቱን ትብብር የበለጠ ማጠናከር የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመደገፍ ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይ አልሚ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አማራጮቻቸውን እያስፋፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮቻቸውን የበለጠ እንዲያሰፉ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር የበለጠ በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።